⚖️MHAAGJ⚖️
-
የሙስና ወንጀል ምንነት፣
የሙስና ወንጀል አፈጻጸም ከአገር አገር፣ ከቦታ ቦታ እና ከባህል ባህል የሚለያይ በመሆኑ በተለያዩ ምሁራን የተለያየ ትርጉም ሲሰጠዉ ይሰተዋላል፡፡ በዚህም የተነሳ የተለያዩ ፀሀፊዎች ስለሙስና ምንንት የተለያየ ትርጉም ሰጥተዋል፤ ሁሉንም ትርጉሞች መተንተን የጽሁፉ አላማ ባይሆንም ለማሳያ ያህል የተወሰኑት እንደሚከተለዉ ቀርበዋል፣
- ሙስና ማለት በአደራ የተሰጠ ስልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል ነዉ (ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል)
- ሙስና ማለት አደራን አለመጠበቅ፣እምነት ማጉደል ወይም አለመታመን፣በጉቡ በምልጃና በአድሎ ሀቅን፣ዉሳኔን ወይም ፍትህን ማዛበት ነዉ (ብላክስ ሎዉ መዝገበ ቃላት)፤
- ሙስና ማለት ለግል ወይም ለቡድን ጥቅም ሲባል ስርዐቶችን፣ ህጎችን፣ደንቦችን፣ አሰራሮችን ወይም/እና መርሆዎችን የመጣስ ማንኛዉም ተግባር ነዉ (የሙስና ቅኝት በኢትዮጵያ 1993)፤
- ሙስና ማለት በግል ወይም በቡድን፣ በፖለቲካ መሪዎች ወይም በቢሮክራቶች ስልጣንና ሀላፊነትን መከታ በማድረግ የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት ለግል ጥቅም የማዋል ኢ-ስነምግባርዊ ድርጊት ሲሆን፤በመንግስትና የህዝብ ሀብትና ንብረት ላይ ስርቆት፣ ዝርፊያ እና ማጭበርበር መፈፀም፤ህግና ስርዐትን በመጣስ በዝምድና፣በትዉዉቅ፣በፖለቲካ ወገንተኝነት፣ በጎሰኝነት፣በሀይማኖት ትስስር ላይ ተመርኩዞ አድሎ መፈፀም፣ፍትህን ማጓደል እና ስልጣንና ሀላፊነትን አላግባብ በመጠቀም ህገወጥ ጥቅም ማግኛ ነዉ (ኬምቤሮናልድና ሰርቦረዌል 2000)
-
የሙስና መንስኤዎች
ሙስና እንዲፈጠርና እንዲስፋፋ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ምክንያቶች አሉ፣የተወሰኑትን ለማየት ያህል፡-
2.1. ከሰዎች አመለካከት/ባህሪ ጋር የተያያዙ ምክንያቶች፣
ስዎች የተለያየ ባህሪ ያላቸዉ መሆኑ ግልጽነዉ፣ስስት ሁሉም ነገር ለኔ ባይነት፣ሳይሰሩ በአቋች ለመበልጸግ መፈለግ፣በአጠቃላይ ከመልካም ስነምግባር ዉጭ መሆን ለሙስና መፈጠርና መስፋፋት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፣
2.2. ከህግ ማዕቀፍ ጋር የተያያዙ ምክንያቶች
የወንጀል ህግ አንዱ ዋነኛ አላማና ግብ ለጠቅላላዉ ትቅም ሲባል አገሪቱን መንግስት፤የህዝቦቹን፤የነዋሪዎቹን፣ሰላም፣ደህንነት፣ ስርዓት፣መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ሲሆን፤ስለወንጀሎችና ስለቅጣታቸዉ በቅድሚያ በማስጠንቀቅ፣ማስጠንቀቂያዉ በቂ ባልሆነበት ጊዜ አጥፊዎችን በመቅጣት ከጥፋታቸዉ እንዲማሩ ማድረግና ለሌሎችም ማስተማሪያ እንዲሆኑ በማድረግ ወንጀልን መከላከል ነዉ፡፡ይህ አዉን ይሆን (ሙስናን መዋጋትና አጥፊዎችን ማስቀጣት) ዘንድ የሙስና ድርጊትን ወንጀል የሚያደርጉና ለወንጀሉ ተመጣጣኝ ቅጣትን የሚጥሉ ህጎች ሊኖሩ የግድ ይላል፡፡የተሟላ ህግ ከሌለ ለሙስና በር ይከፍታል፡፡
2.3.ከተጠያቂነት ጋር የተያያዙ ምክንያቶች
ተጠያቂነት ከሌለ ማንም ሰዉ ያሻዉንና የፈቀደዉን እንዲሰራ ምክንያት ይሆናል፡፡አንድ ሰዉ ያሻዉን ሲሰራ የማይጠየቅ ወይም ቁጥጥር የማይደረግበት ከሆነ ደግሞ ሙስና ይከሰታል፡፡
- የሙስና ወንጀል ልዩ ባህሪያት፣
ወንጀል በአንድ ተወሰነ የህብረተሰብ የእድገት ደረጃ እንደተፈጠረና ከህብረተሰብ እድገት ጋር እያደገና እየተወሳሰበ እንደመጣ ይታመናል፣ በተለይም በአዉሮፓ ከነበረዉየኢንዱስትሪ አብዮት ቦኋላ ከዚህ በፊት ከሚታወቁት ወንጀሎች ሌት ያሉ ወንጀሎች እንደተፈተሩ ነገራል፣የሙስና ወንጀልም ከነዚህ አንዱ ነዉ፡፡ የሙስና ወንጀል ነባር ከሚባሉት የወንጀል አይነቶች (ለምሳሌ ስርቆት፣ ድብደባ፣ አስገድዶ መድፈር ወዘተ.) የተለየና ዉስብስብ እንደሆነ ይገለጻል፡፡የዚህን ወንጀልን ከሌሎች የተለመዱ ወይም ነባር ወንጀሎች የተለየ የሚያደርጉትን ልዩ ሁኔታዎች ማወቅ ሙስና ወንጀልን ለመመርመር፣ለማጋለጥ፣ለመመርመር፣ለመክስስና እጥፊዎችን ለመቅጣት አስቸጋሪ እንዲሆን የሚያደርጉትን ሁኔታዎች ለመረዳትና የተለየ ስልት ለመቀየስ ይረዳሉ፡፡ስለሆነም ሙስና ወንጀል ነባር ከሚባሉት የወንጀል አይነቶች ልዩ የሚያደርጉት ነጥቦች እንደሚከተለዉ በዝርዝር ቀርበዋል፡፡
3.1 የአፈጻጸሙ ስልት፣
በዋናነት የተለመዱ ወይም ነባር የሚባሉት ወንጀሎች ከፍተኛ ጉጉት ወይም ጥላቻ ዉጤቶች ናቸዉ ማለት ይቻላል፣እነዚህ ወንጀሎች በባህሪያቸዉ ስሜታዊና አብዛኛዉን ጊዜ ሃይልን የሚጠቀሙ ሲሆን ተጠቂዎችም ባብዛኛዉ ግለሰቦች/ቡድኖች ናቸዉ፡፡ ብዙ ጊዜ ከጥላቻ፣ ከቂም በቀል፣ወዘተ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ደግሞ በቀላሉ ለማጋለጥና ለመመርመር ብሎም አጥፊዎችን ለማስቀጣት ቀላል ነዉ በአንጻሩ የሙስና ወንጀል በሰሜት አልያም በጥላቻ ሳይሆን በሚስጥርና በጥንቃቄ የሚፈጸም ነዉ፡፡በዚህም ምክንያት መፈጸሙን ለማወቅ የሚያስችል ምንም አይነት ምልክት ማግኘት አይቻልም፡፡ከዚህ በተጨማሪም በሚስጥር ወይም በጥንቃቄ መፈጸሙ ብቻ ሳይሆን እጥፊዉ ለምርመራ መነሻ ሊሆን የሚችል አሻራ የማጥፋት አቅም ስላለዉም ከነባር ወንጀሎች ለየት ያደርገዋል፡፡
3.2. በሙስና የተሳተፈ ሁሉ በህግ አይን ወንጀለኛ መሆኑ.
ሙስና ባብዛኛዉ ከአንድ በላይ ስዎችን ያካትታል፣ትስስሩ የሚፈጠረዉ በበላይና በበታች ሰራተኛ ወይም በዉሳኔ ሰጭና በዉሳኔ ተቀባይ መካከል ሊሆን ይችላል፡፡እነዚህ ደግሞ ሚስጥሩን የሚያዉቁ ብቸኛ ሰዎች በመሆናቸዉ ለጥቅማቸዉ ሲሉ ማስረጃ ሊሰጡ አይችሉም፤ ከዚህም በላይ ሁለቱም በህግ አይን ወንጀለኞች በመሆናቸዉ ሚስጥሩን ይገፉበታል እንጅ ለማጋለጥ አይችሉም፣ለዚሀ አባባል የጉቦ ወንጀልን በምሳሌነት መዉሰድ ይቻላል፣ ጉቦ ተቀባይ የተሰጠዉን የስራ ሀላፊነት ወይም የህዝብ አደራ ወደጎን በመተዉ ማድረግ የማይገባዉን በማድረግ ወይም ማድረግ የሚገባዉን ባለድረግ ለጉቦ ሰጭ ጥቅም የሚያሰጥ ዉሳኔ ይሰጣል፣ ጉቦ ሰጭም በምትኩ ላገኘዉ ያልተገባ ጥቅም ገንዘብ ወይም የተለየ ጥቅም ለጉቦ ተቀባይ ይሰጣል፣ እነዚህ ሁለቱም በወንጀሉ ፍሬ ተጠቃሚዎች ከመሆናቸዉም በላይ በህግ አይን ወንጀለኞች ስለሚባሉ ሚስጥሩን ለመደበቅ ይገደዳሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ይህን ወንጀል ለማጋለጥ፣ ለመመርመር እና አጥፊዎችን ለማስቀጣት ይከብዳል፡፡
በአንጻሩ ነባር ወይም መደበኛ በሚባሉ ወንጀሎች አፈጻጸም ላይ እንደዚህ አይነት ትስስር ባለመኖሩ ወንጀሉ የተፈጸመበት ተጎጅ ጉዳት ያደረሰበትን ግለሰብ ለፍትህ አካላት ለመጠቆምና ለማጋለጥ በመቻሉ እንደዚህ አይነት ወንጀሎችን ለመመርመርና ለመክሰስ ልክ እንደሙስና ወንጀል አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡
3.3 በወንጀሉ ቀጥተኛ ተጠቂ አለመኖር፣
የተለመዱ ወይም ነባር በሚባሉት ወንጀሎች አጥቂና ተጠቂ ሊኖር ግድ ይላል፣ ከወንጀሉ ሁለቱም ተጠቃሚ ስለማይሆኑ አጥቂ የፈጸመዉን የወንጀል ድርጊት ተጠቂ ስለሚያጋልጠዉ ወንጀሉን ለመመርመርና አጥፊዉን ለማስቀጣት ብዙም ችግር ላይገጥም ይችላል፡፡
በሙስና ወንጀል ግን ሁለቱም ተዋንያን ከወንጀሉ ተጠቃሚ ሊሆኑ ወይም በወንጀል ድርጊቱ ሊረኩ ይችላሉ፣ በወንጀሉ የተጠቀመ ወይም የረካ ሰዉ ደግሞ መደበቁን ይገፋበታል እንጅ ሊያጋልጥ አይችልም፡፡ስለሆነም በዚህ ምክንያት የሙስና ወንጀል ከመደበኛ ወይም ነባር ከሚባሉት የወንጀል አይነቶች በእጅጉ ይለያል::
3.4 የወንጀል አፈጻጻም ተግባራቸዉ እንዳይታወቅ ማድረግ በሚችሉ መፈጸሙ፣
በሙስና ወንጀል የሚሳተፉ ሰዎች ህጉንና አሰራሩን የሚያዉቁ በመሆኑ አፈጻጸማቸዉ ከህግ ጋር ግጭት በማይፈጥርበት ሁኔታ ሽፋን በመስጸት ሊከናወን ይችላለል፣በረቀቀና በተቀነባበረ ዘዴ ወንጀሉን ስለሚፈጸሙ ወንጀሉን በቀላሉ ማጋለጥ የሚቻል አይሆንም።
-
የሙስና ወንጀል የምርመራ ስነስርዓት በኢትዮጵያ ህጎች መሰረት
አገራችን አለም አቀፍና አህጉራዊ የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽኖችን የተቀበለች በመሆኗ
በርካታ እርምጃዎች ከሞላ ጎደል አድርጋለች፡፡ከወሰደቻቸዉ እርምጃዎች መካከል የሙስና ወንጀሎችን በግልፅ መደንገግ አንዱና ዋነኛዉ ነዉ፡፡
በአገራችንም እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ የሙስና ወንጀልን ሊተረጉም የሚችል ግልፅ ድንጋጌ ባይኖርም የሙስና ወንጀል ሊባሉ የሚችሉ እንደጉቦና በስልጣን አለአግባብ መገልገል የመሳሳሉት በ1949 ዓ.ም ስራ ላይ በዋለዉ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ዉስጥ ተደንግገዉ ነበር፡፡ ይህንና እነዚህ ድንጋጌዎች የተሟሉ ካለመሆናቸዉም በላይ የሚጥሉት ቅጣት እጥፊዎችን ሊያርም የሚችል አልነበረም፣ በደርግ ስርዐትም ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ (አዋጅ ቁጥር 8/67 እና 214/74) ወጥቶ የነበረ ቢሆንም ልክ እንደ 1949 የወንጀለኛ መቅጫ ህግ የሙስና መገለጫ የሆኑ ጥቂት ወንጀሎችን ከመደንገግ ባለፈ የተሟላ አልነበረም፡፡
በ1949 የወጣዉ የወንጀለኛ መቅጫ ህግም ሆነ በደርግ ስርዐት የወጣዉ ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ የሙስና ወንጀሎች የትኞቹ ሊሆኑ እንደሚችሉ በግልጽ ለይተዉ ያላስቀመጡ እና የተሟሉም ባለመሆናቸዉ እንዲሁም ይህን ሊያሳይ የሚችል ሌላ ህግ ባለመኖሩ የፌደራል የስነምግባርና የጸረሙስና ኮሚሽን መቋቋምን ተከትሎ ሙስና ወንጀሎችን ቢያንስ በትርጉም ደረጃ ሊሰበስብ የሚችል ልዩ የስነስርዐትና የማስረጃ ህግ ሊወጣ ችሎ ነበር፤(አዋጅ ቁጥር 236/93 )፡፡ ይህ አዋጅ በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሙስና ወንጀል ትርጓሜ እንዲሰጠዉና በስራ ላይ በነበሩት የወንጀል ህጎቻችን ዉስጥ ከሚገኙ ድንጋጌዎች መካከል የሙስና ወንጀል ሊባሉ የሚችሉትን ለማስቀመጥ የቻለ የመጀመሪያዉ ህግ ሊሆን ችሏል::
በዚህ አዋጅ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 1 ስለሙስና ወንጀል የተሰጠዉ ትርጓሜም የሚከተለዉን ይመስላል፦
“የሙስና ወንጀል ማለት ከመንግስት ወይም ከህዝብ አገልግሎት ወይም ከህዝብ ጥቅም ጋር በተያያዘ የሚፈጸም ማናቸዉም ወንጀል ሆኖ የተመደበበትን የመንግስት ወይም የህዝብ አገልግሎት ስራ ያለአግባብ በመተጠቀም ለራስ ወይም ለሌላ ሰዉ ወይም ለቡድን ጥቅም መጠየቅ፣ የተስፋ ቃል መቀበል ወይም ማግኘት ወይም ሌላዉን ሰዉ መጉዳት ሲሆን መደለያ መቀበልን፣ጉቦን፣ የማይገባ ጥቅም መቀበልን፣በስልጣን መነገድን፣ በስልጣን ያለአግባብ መገልገልን፣የመንግስት ስራ ወይም የህዝብ አገልግሎት ስራን ለግል ጥቅም በሚያመች አኳኋን መምራትን፣በስራ ተግባር ላይ የሚፈጸም መዉሰድና መሰወርን፣በመንግስት ስራ ላይ ሆኖ በማስገደድ መጠቀምን እና ሚስጥር ማባከንን እና የመሳሳሉትን ሌሎች ጉዳዮች ይጨምራል”
ይህ ትርጓሜ ጉቦ መስጠትና ማቀባበልን እንዲሁም አዳዲስ የሚከሰቱ እንደ መኒ ላዉደሪንግ የመሳሳሉትን ወንጀሎች የማያካትት ከመሆኑም በላይ “….የመሳሳሉትን ሌሎች ጉዳዮች ይጨምራል” ተብሎ የተቀመጠዉ አረፍተ ነገር በክስ አቀራረብና ዉሳኔ አሰጣጥ ላይ መቋጫ የሌለዉ የትርጉም ልዩነት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
አሁን ደግሞ ከግንቦት 1 ቀን 1997 ስራ ላይ እንዲዉል የተደረገ አዲስ የወንጀል ህግ በአገራችን ወጥቷል፤በዚህ የወንጀል ህግ ዉስጥ ስለሙስና ወንጀል ቀጥተኛ ትርጉም ተቀምጦ ባናገኝም ወንጀሉ በመንግስት ሰራተኛ ወይም በማንኛዉም ሰዉ ሊፈጸም የሚችል መሆኑን (በአንቀጽ 404/3) እና ከወንጀል ህጉ ክፍሎች ዉስጥ የሙስና ወንጀል ሊባሉ የሚችሉት የትኞቹ ድንጋጌዎች እንደሆኑ በማያሻማ መንገድ ተቀምጠዋል፤(አንቀጽ 404/4)፡፡ በዚህ ህግ አወቃቀር መሰረት የሙስና ወንጀል ተብለዉ የተለዩት 23 አንቀጾች ብቻ ናቸዉ፡፡ እነዚህ የሙስና ወንጀሎች በመንግስት ሰራተኛ (አንቀጽ 407 እስከ 419፣676/1 እና 696/ሀ)፣ከመንግስት ስራ ጋር በተያያዘ በሌሎች ሰዎች(አንቀጽ 427 እስከ 431) እንዲሁም በማናቸዉም ሰዉ (አንቀጽ 379?፣468 እና 684) ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ከወንጀል ህጉ ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል፡፡
በወንጀል ህግ በመንግስት ስራ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በሚለው ምእራፍ በአንቀጽ 404 በተደነገገው መርህ ንኡስ አንቀጽ (3) የሚከተለውን እናገኛለን፡፡
«ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የማይገባ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ በተሰጠው ሀላፊነት ወይም ተግባር ማድረግ የሚገባውን እንዳያደርግ ወይም ማድረግ የማይገባውን እንዲያደርግ፣ ከሌላ ሰው ላይ ጥቅም የተቀበለ ወይም የጠየቀ፣ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም ለማስገኘት የተሰጠውን ስልጣን ወይም የህዝብ አደራ ያለአግባብ የተገለገለበት እንደሆነ ወይም ማንኛውም ሰው ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማሰብ ለመንግስት ሰራተኛ የማይገባ ጥቅም ለመስጠት ቃል የገባ ወይም ያቀረበ ወይም ለማቅረብ የተስማማ እንደሆነ ወይም በአግባቡ ለተፈጸመ ወይም በአግባቡ ወደፊት ለሚፈጸም የመንግስት ስራ የማይገባ ጥቅምን ማንኛውም ሰው የሰጠ ወይም ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ የተቀበለ እንደሆነ፣ በዚህ ርእስ የተመለከቱትን የሙስና ወንጀሎች አድርጓል ተብሎ ከዚህ በታች በተጻፉት ድንጋጌዎች የተመለከተው ቅጣት ተፈጻሚ ይሆንበታል፡፡
5. የወንጀል ምርመራ፣ ክስ አመራር፣አካሄድና ዋስትናን በተመለከተ፦
የወንጀል ምርመራ፣ ክስ አመራር፣አካሄድና ዋስትናን በሚመለከት በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርአት መጽሐፍ ከተመለከተው ውጭ አንዳንድ በባሕሪያቸውና አፈፃፀማቸው ለየት ይላሉ የሚባሉ ወንጀሎችን የምርመራ የማስረጃ አሰባሰበና ክስ አቀራረብን የሚደነግጉ የሥነ ሥርአት ድንግጌዎች አሉ፡፡
ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በአዋጅ ቁጥር 434/1997 የወጣው የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርአትና የማስረጃ ሕግ ነው፡፡ ይህን በዚህ ክፍል እንመለከተዋለን፡፡
በዚህ አዋጅ በአንቀጽ 7 ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለማየት ሥልጣን የተሰጣቸው የፌዴራል ጠቅላይና ከፍተኛ ፍ/ቤቶች ሲሆኑ በክልሎች ደግሞ የክልል ጠቅላይና ከፍተኛ ፍ/ቤቶች ናቸው እንዲሁም ከሙስና ወንጀል ጋር በተያየዘ የሚነሱ የመያዝ፣ የብርበራ፣ የቀነ ቀጠሮ፣ በማረፊያ ቤት የማቆየት፣ የዋስትና የእግድ እንዲሁም ከምርመራ ጋር የተያያዙ ሌሎች ተመሣሣይ ጉዳዮች የሚታዩትም በእነዚሁ ከላይ በተጠቀሱት ፍ/ቤቶች መሆኑ በአዋጁ ተመልክቷል፡፡
የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርአትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁ. 434/97 አንቀጽ 4 በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት እንዳላቸው በመርሕ ደረጃ ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን በሙስና ወንጀል የተከሰሰ ሰው ወንጀሉ ከ10 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና ሊለቀቅ እንደማይችል አንቀጽ 4/1/ ይደነግጋል፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 4/2/ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ ቁ 28 ከተመለከተው ጋር ተመሣሣይ ሲሆን መርማሪው አንድን በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘን ሰው የዋስትና ወረቀት አስፈርሞ ስለሚለቅበት ሁኔታ የሚዘረዝር ነው፡፡