መንደርደሪያ
ይህን ሥርዓተ-ችሎት (Bench-Book) ለማዘጋጀት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት በዕለት ተእለት የችሎት አካሄድ ሥርዓት ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሁኔታዎችን ዳኛው በቀላሉና በፍጥነት ሊፈታ የሚችልበትን ማጣቀሻ (guideline) ለማዘጋጀት ነው:: ሥርዓተ-ችሎቱ መደበኛውን የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ የሚተካ አይደለም፡፡ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕግ ውስጥ የተካተቱትን ጉዳዩች በሙሉ የያዘም አይደለም፡፡
የዚህ ሥርዓተ-ችሎት ዋና መሠረት የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጉ ሆኖ ነገር ግን ፡-
1. በሥ/ሥርዓት ሕጉ ውስጥ የተካተቱ ሆነው ነገር ግን ጠቅለል ባለ አገላለፅ የተደነገጉ በመሆናቸው ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮችን ለማብራራት ተሞክሯል፡፡
2. በሕጉ በግልፅ ያልተሸፈኑ ነገር ግን በዕለት ተዕለት የፍ/ቤቶች ሥራ ውስጥ በብዛት የሚያጋጥሙ የሥነ ሥርዓት ጉዳዮችን በተመለከተ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ጥረት ተደርጓል፡፡
3. በሥነ-ሥርዓት ሕጉ የተሸፈኑ ሆነው ነገር ግን በአተርጓጎምና በአተገባበር ረገድ በፍ/ቤቶች ወይም በዳኞች መካከል ልዩነት የሚታይባቸውን ዋና ዋና የሥነ-ሥርዓት ጉዳዩች በተመለከተ በተቻለ መጠን ልዩነቶቹ የሚጠቡበትንና ሕጎቹ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚተረጐሙበትንና የሚተገበሩበትን አቅጣጫ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡
ከላይ እንደተገለፀው የሥርዓተ-ችሎቱ ዋና መሠረት የሥ/ሥርዓት ሕጉ ቢሆንም ማብራሪያ የሚሹ ነጥቦችን ለማብራራትና ክፍተቶችን ለመሙላት ግን ልምድ ያላቸው ዳኞችን፣ ጠበቆችንና ሌሎች የሕግ ሰዎችን በቃልና በፅሑፍ በመጠየቅና በማማከር የተገኙ ሐሳቦች እንዲሁም የሌሎች ሀገሮች ልምዶች እንደመነሻ ሐሳብ በጥቅም ላይ ውለዋል፡፡
ሥርዓተ-ችሎቱ እንደ ሕግ አዛዥነት ባይኖረውም እንደቀላል ማጠቀሻ፣ እንደማብራሪያና እንደ ክፍተት መሙያ ግን ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመናል፡፡